ምንም መዋሸት አያስፈልግም ተኝቼ ህልም ካየሁ ያለምኩት ስላንቺ ነው:: ያላለምኩሽ ቀን መተጣጣታችንን እቃዣለሁ:: ቅዠቴን “በስመ አብ” ብዬ አባርሬ ስነቃ አልጋዬ አጠገብ የተሰቀለው ፎቶሽ መለየትሽን ይነግረኛል::
ታስታውሻለሽ “ ’ሁለት አንድ አይነት ላባ ያላቸው ወፎች አብረው ይበራሉ!’ ስትዪኝ አንዳቸው ቀድመው እስካልደከማቸው ድረስ” ያልኩሽን!? አሁን አንዳችን ቀድሞ ታክቶናል:: የአንዳችን ላባ ቀድሞ መርገፍ ጀምሯል፤ ምናልባትም እረግፏል:: አንቺ ቀድመሽ ደክሞሻል:: እናም ማነሽ ሁለት አንድ አይነት ላባ ያላቸው ወፎች አብረው የሚበሩት አንዳቸው ቀድመው እስካልደከማቸው ድርስ ብቻ ነው!
መቼም ካስታወስሽ ሞትን በጣም ትፈሪ ነበር:: ለምን ትፈሪያለሽ ስልሽ ከምክንያት በላይ ነበር ፍራቻሽ:: አሁን አሁን ሳስበው ሞትን የማይፈራ ማንም የለም:፡ ሞት ለምን እንደሚያስፈራ ታውቂያለሽ!? ከሌሎች ስለሚያሳንስሽ ብቻ ነው:፡ እስኪ አስቢው ለአይንሽ የምትጠዪው ጠላትሽ ቀርቶ አንቺ “ይሄን ያህል ከኖርሽ ቢበቃሽስ? ባትናገርም የተሸከመችሽ ምድርም ትሰለቻለች እኮ!” ስትባዪ:: እናም ማነሽ ሞትን ትፈሪ የነበረው ካንቺ በኋላ ያለውን ቀጣይ ህይወት ያለማየትሽ ስለሚያስቀናሽ ነበር::
በርግጥ ሞት የእኔ ከምትያቸው ሁሉ ሊለይሽ ይችላል:: ነገር ግን ሰው ሞትን የሚፈራው ከሚወዳቸው ስለሚለየው ብቻ አይደለም፤ ከሞተ በኋላ ያለውን ህይወት ስለሚያስብ እንጂ::
ማነሽ ሳትዋሺኝ… የዛሬ ስድስት ወር በእኩል ሰዓትና ደቂቃ የሰው ዘር በሙሉ ለዘላለም ያንቀላፋል ቢባል ሞትን የሚፈራ ይኖራል ብለሽ ትገምቻለሽ!? ከነተረቱስ “ባገር የመጣ” አይደል የምንል? … አየሽ ሞትን ትፈሪ የነበረው በተናጠል ስለሚመጣ ብቻ ነው:: የዛሬ ስድስት ወር የሰው ዘር በሙሉ ያንቀላፋል ከ… በቀር ቢባል ግን ሁሉም አንደበቶች ስለማያንቀላፋው አንድ ሰው በማውራት የቀረቻቸውን ስድስት ወር ይፈፅሟታል::
ወደ ቀደመ ሃሳቤ ልመለስ… ሞኝ ከመሰልኩሽ ቀሪ እድሜሽን ሙሉ ስትስቂ መኖር ትችያለሽ እውነቴን ነው የምልሽ ዛሬም በሬን ሳልዘጋ ነው የምተኛው:: ለምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? የምሽቱ ቀዝቃዛ ንፋስ ገፍቶ ከመኝታዬ ቢያመጣሽ ብዬ ነው። ግን ቅዝቃዜው ገላዬን ከማኮማተር ውጪ ያተረፈልኝ ነገር የለም::
ክረምት ሆኖ ሰማዩ ሲጠቋቁርና ደመናው ጠብ እንደፈለገ ጎረምሳ ሲንጎማለል አንኳር ሆኖ እንደሚዘንበው ጠብታ ዝናብ ደጄ ላይ ትወድቂያለሽ ብዬ እናፍቃለሁ:: ናፍቆቴ ግን ተስፋ ቢስ ነው::
ጥንድ ጥንድ ሆነው የሚሄዱ ፍቅረኛሞች ስመለከት “ አቤቱ የፍቅር አምላክ ከነዚህ ጥንዶች ስንቶቹ ይሆኑ ተቃቅፈው በሄዱበት ጎዳና ተቃቅፈው የሚመለሱ!?” ብዬ እጠይቃለሁ:: ማነሽ… እኛ በሄድንበት ጎዳና አልተመለስንም አይደል?
ትዝ ይልሻል አንዴ “ዝንብን የምታክል ፍጥረት ያውም ከአንድ ቀን ያልበለጠ እድሜ ያላት ፈጠኖ ሟች በትንሽ እድሜዋ ለሰው ልጅ ጤና ጠንቅ ስትሆን” ያልሽኝንና የሚወራ ጠፍቶ ስለዝንብ እድሜና ስለጠንቀኝነቷ እያወራን የተደመምንው!? ማነሽ እኔ ልሙት ፍቅር ካለ እኮ ስለዝንብ እድሜም እያወሩ በፍቅር አይን ሲተያዩ መዋል ይቻላል::
ማነሽ ሙች! … ሰው ራሱ ዝንብ ነው! ሰው በእግዚአብሄር አይን ቁልቁል ሲታይ የማራቶን እሯጭ ነው:: ምናልባትም ውድድሩን መጨረስ አቅቶት አቋርጦ የሚወጣ እድለቢስ:: ለነገሩ ሮጦ የፍፃሜው ክልል ገባ ማለት “አፈር ነህና …” ተባለለት ማለት ነው:: እውነቴን እኮ ነው ያውም ከታደልሽ እኮ ነው ሁለት ሰሃት የምትሮጪው:፡
እስኪ አስሊው! የምድር አንድ ሺህ አንድ መቶ አመት በእግዚአብሄር ዘንድ አንድ ቀን አይደል!? ትንሽ ጊዜ ሰጥተሽ ብታሰዪው በእግዚአብሄር አንድ ሰሃት ማለት ምን ያህል ዘመን ማለት እንደሆነ ይነግርሻል:፡ አየሽ አንቺም ዝንብ ነሽ! የመለማመጃ ጊዜ የሌለው የማራቶን ሯጭም ነሽ:: ማራቶንሽን ሁለት ሰሃት ከምናምን አጠናቀቅሽ ማለት የተንዘላዘለ እድሜ ኖርሽ ማለት ነው::
አየሽ በዚች ሁለት ሰሃት በማትሞላ እድሜያችን ነው ጉዳንጉዳችንን ሁሉ ከውነን የምናሸልበው:: ተመልከቺ እስኪ ማነሽ… ትምህርት፣ ስራና ትዳር ከነዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ክህደትና መታመን፣ ማጣትና ማግኘት፣ በቀልና ምህረት እና ሌሎች ጉዳዮቹን በፍጥነት መከወን- ከሁለት ሰሃት በፊት::
ማነሽ! ዝም ብዬ ስዘላብድ እኔም ወደ መጨረሻው የመሮጫ መስመር ደረስኩ ይሆን እንዴ!? ማነሽ ግን አንቺ እንዲህ የዘላበድኩልሽ!? የኔ ወፍ ማነው ስምሽ ግን? ስምሽ ቢጠፋኝም ስሜ ቢጠፋሽም ቃላት ከሚገልፁት በላይ አፈቅርሻለሁ:: ማን ያውቃል አብረን ማራቶናችንን እንፈፅም ይሆናል! ማን ያውቃል “የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ” አይደል የሚባል!? ምንድን ነው የሚያዘላብደኝ? አልተሻለኝም ማለት ነው!?
ለአንቺ - ለማነሽ!
No comments:
Post a Comment