ፍቅር የደስታና የትፍስህት ምንጭ እንጂ የስብራት ምክንያት እንዲሆን አልተፈጠረም:: ታዲያ ውስጡ ዘልቀን ስንገባ በደስታ የተዋጥነውን ያህል ያፈቀርንው ሰው ሲተወን ልባችን ይሰበርና ቅስማችን ምስቅልቅሉ ይወጣል:: ከፍቅረኛዎ ጋር አብረው እያሉ ያሰቡዋቸው እና የተለሟቸውን ውጥኖች መልሶ ማሰቡ ያምዎታል:፡አሁን እርስዎ ብቻውን የሚበር ርግብ ሆነዋል:: ዘላለም በአብሮነት የሚዘልቅ የመሰሎት የፍቅር ህይወትዎን በአጭሩ ተቀጭቷልና ሁሉ ነገር የውሸት ይሆንብሆታል:: በዚህ ሰሃት የሚያስቡት ነገር ቢኖር ቁርጥራጭ ትዝታዎችን ከውስጥዎ እንዴት ነቅሰው እንደሚያወጡ ብቻ ነው:: በፍቅር ላይ ፊትዎን ሳያዞሩ የተሰበረ ልብዎን እንዴት ሊጠግኑ እንደሚችሉ ያወጣሉ ያወርዳሉ:: ታዲያ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆነው ደግሞ ወደ ፍቅር ህይወት ውስጥ ለመመለስ ቀርቶ ራሱ ፍቅር መጥቶ የልብዎን በር ቢያንኳኳ ለመክፈት ፈቃደኛ አይሆኑም:: ለምን ቢሉ የተነጠቁት የፍቅር ህይወት “ፍቅር” የሚባለውን እሳቤ ጥላሸት ቀብቶታልና ነው:: በዚህ ስሜት ውስጥ ሆነው ከዘለቁ ምናልባትም ለህይወትዎ የሚመች ጥሩ አፍቃሪ ቢያገኙ እንኳን ዳግም ልብዎን ሊሰጡት አይፈቅዱም:: ግና ውስጥዎ ዳግም ታድሶ የልብዎ በር ለፍቅር ክፍት ይሆን ዘንድ የተሰበረ ልብዎን የሚጠግኑባቸው አምስት ጤናማ መንገዶች አሉና ይሞክሯቸው::
ልብዎ ከፍቅረኛዎ መለየቱን አምኖ እንዲቀበል ያድርጉ
ልብዎን ከፍተው የሰጡት ሰው ቢከዳዎት አለም ሁሉ የከዳዎት አይምሰሎት:: ወደ ኋላ መለስ ብለው ከፍቅረኛዎ ጋር ያሳለፉዋቸውን ወርቃማ ጊዜያት ማሰቡ ውስጥዎን በሰቀቀን ሊጨርስ እንደሚችል ግልፅ ነው:: ታዲያ ይህ ስሜት እያደር ውስጥዎ ዘልቆ ሙሉ በሙሉ ከአለም የተገለሉ ብቸኛ ፍጡር ሊያደርጎት እንደሚችል አይርሱ:: ስለዚህ ባሳለፉት መጥፎ ትዝታ ተገፍተው ብቻዎትን ሊቀሩ አይገባም:: ከዚህ ይልቅ ውስጥዎን ያቆሰለውን የመለየት ህመም ፊት ለፊት ተጋፍጠው ካለፈው የሚማሩበትን ቀና መንገድ መጓዙ ይሻላል:: እንዲህ ባለው ሁኔታ በእያንዳንዱ ትዝታዎ ላይ የበላይ መሆንዎ ለቀጣይ ህይወትዎ የሚያምንና የሚያፈቅር ሙሉ ልብ እንዲኖሮት ያደርጋል:: አንድ ነገር አይርሱ ዛሬ ያልተጋፈጡት የሚያምር የፍቅር እውነታ ነገ ፍርሃትን ይወልዳል:: ፍርሃት ደግሞ እምነትን ያጠፋል:: እምነት የሌለው ልብ ደግሞ ሊያፈቅር አይቻለውም:: በዚህ ሰሃት እውነትን ሲጋፈጡ አቅም ሊያንሶትና ደጋግመው ወደ ውስጥ ሊያለቅሱ ይችላሉ:: ግን ነገ ጥሩ አፍቃሪ የሚሆነው ልብዎ ያመሰግኖታል::
ንዴትዎን የሚያበርዱበት ጤናማ መንገድ ይፈልጉ
አሁን ማድረግ የሚፈልጉትን ጠንቅቀው ያውቃሉ:: ግን እንዴት ማድረግ እንዳለብዎት ግልፅ መንገድ አላገኙም:: አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች ጋር ተቀላቅለው ደስተኛ ለመምሰል ከመታገል እቤትዎ ቁጭ ብለው ቴሌቪዥን ላይ ማፍጠጥ ሊቀሎት ይችላል:: ይሄ አንዳንዴ ከራስዎ ጋር ለመነጋገር ስለሚረዳ ጥሩ ቢሆንም ማህበራዊ ግንኙነትዎን ማጠንከሩ ግን በውስጥዎ ሰላም ለመፍጠር ስለሚረዳዎት አስፈላጊ ነው:: ወደዱም ጠሉም ከጓደኞችዎ ጋር መገናኘትዎ ከፍቅረኛዎ ጋር በመለየትዎ የደረሰብዎትን ጭንቀት ለማስወገድ ይረዳዎታል:: እንዲህ የተለያዩ አጋጣሚዎችን ተጠቅመው ጊዜዎትን ከሰዎች ጋር ማሳለፍ በጣም ተመራጭ ነው:: ጭንቀት ወደ ተስፋ መቁረጥ እንደሚያመራ አይርሱ:: ተስፋ መቁረጥ ደግሞ ወደ ንዴት አምርቶ አጉል ያደርጋል:: ከፍቅረኛዎ ጋር መለየትዎ እንዲያሸንፍዎት አይፍቀዱ:: የካደዎት ፍቅረኛዎ ደህና መሆንዎን በሚገባ ሊያውቅ ይገባል:: ነገሩ ነው እንጂ… አይነት መሆኑ ነው::
ለራስዎ ክብር ይኑርዎት
ፍቅረኛዎ በእርስዎ ላይ ኃይል የሚኖረው እርስዎ የሰጡትን ያህል ነው:: ከተለያዩ በኋላ ስለራስዎት መጥፎ ካሰቡና ራስዎን ከጣሉ ከፍቅረኛዎ መለየቱ ልብዎን ብቻ ሳይሆን ነፍስዎትንም አኝኮ በልቶታል ማለት ነው:: ለሁሉም ጊዜ አለውና ከጊዜ ጋር የተሰበረ ልብዎ አብሮ ይጠገናል:: መንፈስዎና ነፍስዎ ከውስጥዎ ከጠፋ ግን መልሶ ማግኘቱ አስቸጋሪ ነው:: ሁልጊዜ ደስታ ይሰማዎት:: ፈገግታ ከፊትዎ አይጥፋ:: ለራስዎ ያልዎትን ፍቅር በተለያየ መንገድ ይግለፁ:: በጎ በጎ ነገሮችን ያስቡ:: አንድ ነገር ደጋግመው ለራስዎ ይንገሩት፤ ከከዳዎት ፍቅረኛዎ ውጪ ሙሉ ሰው ሆነው ሊኖሩና ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ መሆንዎን::
ውስጥዎ ያለውን ስሜትዎን ከሰው ጋር ያውሩት
በጣም አስቸጋሪው ነገር ህመምዎን ውስጥዎ አፍነው መያዝዎ ነው:: በውስጥዎ ታፍነው የሚቀመጡ የሚጎዱ ሃሳቦች ያስጨንቃሉ፣ ግራ ያጋባሉ፣ ያናድዳሉ:: ብቸኛ ያደርጋሉ:: የተለይዎት ፍቅረኛዎ ለእርስዎ ምን ማለት እንደሆነ ሊገባው ለሚችል ጓደኛዎ ጉዳዩን ያውሩ:: ስሜትዎን እንዲህ ሲገልፁ የልብ ስብራትዎ ያገግማል:: ከሚወዱት ሰው መለየትዎ በውስጥዎ የፈጠረውን ስሜት ለጓደኛዎ ሳይደብቁ ይንገሩ:: ከዛ መጥፎ ስሜት ለመውጣት እያደረጉ ያሉትን በጎ እርምጃዎችም ይንገሩዋቸው:: እንዲህ ራስዎን ለጓደኛዎ ግልፅ አድርገው ሲቀርቡ ጓደኛዎትም በተመሳሳይ ስሜት ውስጥ አልፎ ሊሆን ስለሚችል ተጨባጭ የሆነ ምክር ሊሰጥዎት ይችላል:: ይሄ ደግሞ የተሰበረ ልብዎን ለመጠገን ወሳኝ ሚና አለው::
ራስዎን አይደብቁ
ራስዎ ሲረጋጋና ውስጥዎ ዝግጁ ሲሆን ልብዎን ለፍቅር ክፍት ያድርጉ:: ምናልባት ከአዲስ ሰው ጋር ለመጀመርያ ጊዜ ሲገናኙ ውስጥዎ ሊጎዳ ይችላል::ምናልባትም አዲስ የተዋወቁትን ሰው ከቀድሞ የፍቅር ታሪክዎ አንፃር እየመዘኑት ተመሳሳይ እጣ የሚጠብቅዎት እየመሰሎት በጭንቀት ሊሰቃዩ ይችላሉ:: ይሄ አዲስ ነገር ስላልሆነ ብዙ ሊያስጨንቆት አይገባም:: ዋናው መርሳት የሌለብዎት ቁምነገር ትናንት ማለፉን ነው:: ያለፈው ፀፀትዎ የሚከተልዎ ከሆነ ግን ሁሉንም ሰው በአንድ መነፅር ነው የሚያዩት:: ሰውን ለመገመት አይቸኩሉ:: በራስዎ ውስጥ ያለ አንዳች ልዩ ነገር ያንን ሰው ለፍቅር እንደሚጋብዘው አይርሱ:: አብረው ሊሆኑት ስላሰቡት ሰው ስብዕና ለማወቅ ጊዜ ይውሰዱ:: ምናልባት ብዙ የሚጋሯቸው ተመሳሳይ ስሜቶች ሊኖሩ ይችላሉ:: ነገሮች ከዚህ ተነስተው ወዴት ሊወስዱዎት እንደሚችሉ ማን ያውቃል!?
እናም የፍቅር ቁስለኞች የተሰበረ ልብን በመጠገኑ ሂደት ውስጥ ማለፉ ሊከብዳቸው ይችላል:: ዋናው ቁም ነገር ግን ሙሉ ፈቃደኝነትና ከልብ የመነጨ ፍላጎት ብቻ ነው::
No comments:
Post a Comment