እግዚአብሄር ጭቃውን አሰማምሮ ሲጨርስ ትኩር ብሎ ተመለከተው:: የሆነ የጎደለው ነገር እንዳለ ገብቶታል:: “ምንድን ነው ይሄ ጭቃ የጎደለው?” አለ እግዚአብሄር:: ጉድለቱ ጎኑ ላይ ወፍራም ጭቃ መሸከሙ ነበር:: ከወፍራሙ ጭቃ ላይ ቆነጠረለት:: የጭቃው እንከን ተቀረፈ:: አዳም አለው ያንን ርጥብ ጭቃ:: ቡጫቂዋ ጭቃም ሄዋንን ሆነች:: አዳምና ሄዋን የገነት ፀሃይ ላይ ተሰጥተው እያለ ውሻና ድመት ወደነሱ መጡ:: የአዳም አይን ሁለቱም እንስሳት ላይ አረፈ:: የሄዋን ቀልብ ግን ድመቲቱ ላይ ነበር:: ድመት ሄዋንን ጠቀስ አድርጋ ወደ ገነት ዛፎች ስር ይዛት ሄደች:: አዳም እግሩ ስር ተኝቶ ከሚያንኮራፋ ውሻው ጋር ቀረ::
ድመት አዳም እንዳያይ ደኑ ውስጥ ተደብቃ ለሄዋን የተለያዩ ትምህርቶችን አስተማረቻት:: በችግኞች ተከልላ ተፀዳድታ በእግሮችዋ አፈር ጭራ ሸፍና ለሄዋን አሳየቻት:: ሄዋን ነውርንና ሚስጥርን እንዴት ቀብሮ ማስቀረትና ከሌሎች መደበቅ እንደሚቻል ተመለከተች:: ትምህርት አንድ አለች ሄዋን::
አስተምህሮ ድመት ሁለት- ድመቲቱ ምራቅዋን የፊት እግሮችዋ መዳፍ ላይ ቀብታ ፊቷን ዳበስ ዳበስ አደረገች:: ሄዋን መዋብን ከድመት ተማረች:: ድመቲቱ ሄዋንን “ተከተዪኝ” ብላ ወደ ጎጆዋ ሄደች:: ትንሽዋ የድመት ጎጆ ሁለት በር ነበራት:: ሄዋን “ይችን ለምታክል ቤት ለምን ሁለት በር አስፈለገ!?” አለች በርጥብ ህሊናዋ:: ለሄዋን ጥያቄ ግን ድመቲቱ ምላሽ ነበራት:: ወንድ ድመቶችን ሊያማልል በሚችል የውብ ኮረዳ ድመት ድምፅ “ሚሚሚያያያውው ውውው” አለች ድመቲቱ:: አንድ ወደል ድመት ድምፅዋን ሰምቶ መጣ:: የመጣው ወደል ድመት ግን ባልዋ አልነበረም፤ ውሽማዋ እንጂ:: የውሽሜን ነገር ሄዋን ከድመት ተማረች:: በፊት ለፊት የገባው ወደል ውሽሜ ድመት በጓሮ በር ሹክክ ብሎ ሲወጣ ስትመለከት ነው የጓሮ በር ጥቅም ለሄዋን የተገለጠላት:: ሄዋን አንድ ነገር አሰበች “ከአዳም ውጪ ሌላ አዳም ይኖር ይሆን በዚህ ደን!?” ለጥያቄዋ መልስ ባይኖራትም የጓሮን በር ጥቅም በልብዋ አኖረችው:: ወደሉ ድመት አጥር ላይ ተንጠልጥሎ “ሚያው!” አለ በጎርናና የኩራት ድምፅ:: ሄዋን ውሽማን አጥር ማዘለልንም ከድመቲቱ ተማረች:: እነሆ ዛሬ የልጅ ልጅዎችዋ
“መስራቱንማ አቶ ባል ይሰራል
አጥር ዘሎ ሲሄድ ውሽማ ደስ ይላላ” እያሉ ያንጎራጉራሉ::
አዳም እግሩ ስር የተኛውን ውሻ ቀስቅሶ አስነሳው:: ውሻው ዞር ዞር ብሎ አካባቢውን ቃኝቶ ተመልሶ ተኛ:: አዳም አካባቢን መጠበቅ እንደሚገባ ከውሻ ተማረ:: ውሻ ወደ አንድ ጥግ ሮጥ ብሎ ሄዶ ሸና አዳም ይሄንንም ከውሻ ተማረ:: ተስተምሮ ሁለት ማለት ነው:: ዛሬ ግን “አጥር ስር የሚሸና ውሻ ነው” ይባላል::
ጆሮውን አቁሞ አፍንጫውን ወጠር ፈታ እያደረገ በእግሮቹ መሬት ጫር ጫር አድርጎ ደመነፍሱ ወደ መራው አቅጣጫ ሮጠ- ውሻ:: ከእንስት ውሺት ጋር ተጣብቆ ነበር የተመለሰው:: አዳም የድመትን አማራጭ አላየምና የውሻን የአደባባይ ምግባር ወረሰ:: ምስጢር እንዴት እንደሚጠበቅ አለማወቁም ጀብደኛ አደረገው:: በሆነ ባልሆነ የሚጮህ ግልፍተኛ:: የውሻን አስተምህሮና የአዳምን ኩረጃ ተደብቃ ትመለከት የነበረችው ድመት እየሳቀች ወደ ሄዋን ሮጠች:: ሳቅዋ ድመትንም ውሻንም አበሳጨ::
በድመቷ ሳቅ የተበሳጨው ውሻ እስዋ ምን የተለየ ጥበብ ብታውቅ ነው ብሎ ተደብቆ ለማየት ወደ ድመት ጎጆ ሄደ:: የድመቲቱን ጎጆ ሲመለከት አንድ ነገር ከነከነው “ለምን የድመቲቱ ጎጆ ሁለት በር ኖረው !?” አለ ውሻ በመገረም በውሻ ህሊናው:: የድመቲቱን የሁለት በር ሚስጥር ለአዳም ነገረው:: አዳም ለጎጆው:: ሄዋን አዳምን እንዴት አሳምና ጎጆዋ ሁለት በር እንዲኖረው እንደምታስደርግ እያሰላሰለች ከፍራፍሬ ለቀማ ስትመለስ አዳምን በኩራት የጓዳ በሩን ተደግፎ ስትመለከተው ሩጫዬን ሮጠልኝ አለች::
የሄዋን አዳዲስ ባህሪዎችን ማምጣት ያላማረው አዳም ድመት ምን እያስተማረቻት እንደሆነ እንዲሰልልለት ውሾን ላከው:: ውሻ ከድመቲቱ ጎጆ ጀርባ ተደብቆ ድመቲቱ ለሄዋን የምታስተምራትን ለመሰለል አደፈጠ:: ድመቲቱን እንጂ ሄዋንን ማየት አልቻለም ነበር:: ሄዋን የአዳምን ተላላኪ ውሻ አይታ ተደብቃ ነበር:: ውሻ አዳም ያዘዘውን ሊያይ ባለመቻሉ ተስፋ ቆርጦ ሊመለስ ሲል ግራ ቀኝ እየተራመደ የሚመጣ ድመት አየ:: የድመቲቱ ባል እንዳልሆነ አውቋል:: ወደሉ ድመት ተገላምጦ ወደ ድመቲቱ ጎጆ ገባ:: ወደሉ ድመት ምን ሊያደርግ ወደ ሌላ ድመወራ /አባወራ እንደማለት/ ቤት እንደገባ ለማየት ውሾ አድብቶ ወደ ድመቲቱ ጎጆ ተጠግቶ አሾለቀ::
በተመለከተው ነገር ደነገጠ:: አዘነም:: አፈረም:: የድመቲቱን ብልግና ማየቱን ነግሮ ሊሳለቅባት እየሮጠ ወደ የፊት ለፊቱ የድመቲቱ በር ሲዞር ውሽሜ ድመት በጓሮ በር ፈትለክ አለ:: ውሻ በፊት ለፊት በር በአይቼሻለሁ ተኮፍሶ ሲገባ ጎጆው ውስጥ ሄዋንና ድመቲቱ ብቻ ነበሩ:: ውሻ ግራ በመጋባት ተዟዙሮ ቤቱ ውስጥ አነፈነፈ:: ጎጆው ውስጥ የተፈጠረውን ሁሉ አይቷል፤ ነገር ግን ድመቲቱ ምንም እንዳልተፈጠረ ተረጋግታ ተቀምጣለች:: ሄዋንም በድመቲቱ መረጋጋት ተገርማ ነበር የምትመለከታት:: ከድመቲቱ እርጋታ የተማረችው ነገር ቢኖር የልብን ሰርቶ ምንም እንዳልተፈጠረ ተረጋግቶ ማሳለፍ እንደሚቻል ነበር:: ውሻም በስተመጨረሻ የገባው ነገር ውሽሜ ድመት በጓሮ በር ማምለጡ ነበር:: የጓሮ በርን ክፋትና የጓሮ በርን ምስጢር ለመንገር ወደ አዳም ሮጠ::
አዳም “አንድ በር ይበቃዋል ለጎጆአችን!” አላት ሄዋንን በጩኸት:: ሄዋን ሳቅ እያለች “ጎጇችን ሁለት በር ይኑረው ያልከው አንተው ነበርክ እኮ አሁን ምን ተገኘና ” አለች ምን ተገኝቶ አንድ በር ይሁን እንዳለ ብታውቅም:: አዳም የሚመልሰው ሲያጣ ውሻን አፍጦ ተመለከተው:: ውሻ ለአዳም የሚመልሰው ሲያጣ መላ ፍለጋ ወደ ድመቲቱ ጎጆ ሮጠ::
የድመቲቱ ጎጆ ሲደርስ የድመቲቱ ባል የጎጆውን አጥር ከፍ አድርጎ እያጠባበቀ ሲያጥር አገኘው:: ውሻ እያለከለከ ተመልሶ ለአዳም ነገረው:: አዳም ከገነት ደን ዛፍ ቆርጦ የጎጇቸውን ክልል አጠረው:: ግቢውን አጥሮ ሲጨርስ አጥሩ በቂ መስሎ አልታይ ሲለው የጓሮ በር አሰርቶ ሃሳብ የጨመረለትን ውሻውን ልጥ አርሶ ገምዶ አሰረው፤ አጥር የማይመልሰውን ጠላት እንዲጠብቅ:: የውሻም ግቢ ጠባቂነት ያኔ ተጀመረ:: አዳም ጎጆን በአጥር ከልሎ ጠባቂ ውሻ ማሰርን የብልሃት መጨረሻ አድርጎ ቆጠረው:: የረሳው ነገር ግን ነበረ፤ ያም ነገር የሄዋን አማካሪ የሆነችው ድመት ጎጆው ውስጥ መኖሯን ነበር::
ከዚያን ዘመን ጀምሮ ውሻ የጌታው በር ላይ በሰንሰለት ታስሮ በፊት ለፊት ገብተው በጓሮ የሚወጡትን ውሽሞች እያየ መኖር እጣ ፈንታው ሆነ:: በጓሮ በር የሾለከ ውሽማ ባየ ቁጥር በድመት ተታሎ አዳምን ያሰራው የጓሮ በር ይታሰበውና በእንጉርጉሮ ያለቅሳል:: ያንን ውሻ በማለዳ የሚያሰማውን የፀፀት እንጉርጉሮ ለቅሶ አዳም ከንቱ ማላዘን አለው:: ውሻ ግን ባላዘነ ቁጥር በድመት ተታሎ አዳምን ያሰራው የጓሮ በር የሚያሳየውን ፍቅር አልባ ህይወት እያሰበ እግዚኦልኝ ማለቱ ነው::
ታዲያ ውሻ ጌታው ምን ቢበድለው እንኳን ሊከዳው ይሰንፋል:: የሚያሰንፈው የበደለኝነት ስሜቱ ነው:: ያ የበዳይነት ስሜት የጓዳው በር ጉዳይ ነው:: ውሻ የታማኝነት ምሳሌ ሆኖ በአዳም ግቢ ታስሮ ይኖራል:: ውሻ በር ላይ ጋደም ብሎ የጌታውን በር መጠበቁ የጓዳ በር ስህተቱን ማካካሻ ታማኝነቱን ማረጋገጡ ነው::
ድመቲቱ ግን የትም ትለምዳለች:: ሁሉ ቤቷ ነው:: በሁሉም የፊት በሮች ገብታ በሁሉም የጓሮ በሮች ትወጣለች:: አጥር ትዘላለች:: ፍፁም በሆነ መመሳሰል የውሽሜዎች አምሳያ ነች:: የቀን መዝመምን አይታ ላትመለስ ከአሳዳሪዎቿ ቤት ትርቃለች:: ልክ ውበት አይቶ የመጣ ውሽማ ውበት ሲከስም እንደሚሸሸው ማለት ነው:: በውሽሜዎችና በድመቶች መካከል ዘላቂ ፍቅር የለም ዘላቂ ጥቅም እንጂ:: የውሻ ግን ከዚህ ይለያል:: ፍቅሩ እስከ መቃብር ነው:: ታማኝነቱም የዘሩ ነው:: ታዲያ “እንደ ሄዋን
No comments:
Post a Comment