እሷ
ሌሊቱን እንቅልፍ ባይኗ ሳይዞር ነው ያደረችው - ቤርሳቤ:: መስታወት ፊት ቆማ የተለያዩ ልብሶቿን እያቀያየረች ትለካለች:: ሁሉም አልስብ አላት:፡ ጥቁር ሱሪ በጥቁር ቦዲ ለብሳ ሰማያዊ ስካርፕ አደረገች:: ይሄ አለባበስዋን እንደሚወደው ብዙ ጊዜ ነግሯታል:: “ አፍ ውስጥ እንደ ሻኛ ስጋ ይሟሟል” ብሎ የሚያወድስላት ከንፈርዋን በስሱ ቀይ ቀለም ቀባችው::
ለመጨረሻ ጊዜ ራስዋን በመስተዋት ተመለከተች:: የራስዋ መልክ ለራስዋ አማራት:: “በቀጥታ ቢሮው ሄጀ ለምን እንደራቀኝ እጠይቀዋለሁኝ::” አለች::
እሱ
ከሱፍ /ሙሉ/ ልብሶቹ ውስጥ ነጩን መርጦ በጥቁር ሸሚዝ ለበሰ:: ይሄንን አለባበሱን እንደምትወድለት አስታወሰ:: አግኝቷት ምን ሆና እንደዘጋችው ሊጠይቃት ቆርጧል:: “አምስት ቀን ያለበቂ ምክንያት መዘጋጋት?” አለ በመገረም::
እነሱ
የስልኩን መነጋገሪያ አንስቶ አንድ ሰባት ሁለት ዜሮ ጠቀጠቀ ቁጥሮቹን::
“ሄሎ” የሚል ድምፅ ሰማ:: የቤርሳቤ ድምፅ መሆኑ ገብቶታል::
“እኔ ነኝ” አለ ሳያስበው::
“ምን ፈለክ?” አለችው - ቤርሳቤ:: ከተናገረች በኋላ ሰማያዊ ስካርፕዋን የማትፈልገውን ንግግር ያወጣ አፍዋ ውስጥ ጠቀጠቀችው::
“ምን ፈልጌ ነው ልበላት? ቆይ ለምንድን ነው የተራራቅንው ልበላት? እንዲህ ብላት ደግሞ ፍቅር ፀንቶበት ነው ብላ ትኮራለች” አለ ለራሱ::
“ በአንዴ እሺ ብዬ መገናኘት የለብኝም:: ወንዶች ፊት ከሰጧቸው አይቻሉም:: ኩርፊያዬ ሊገባው ይገባል:: ድምፄን ቆጣ አድርጌ ምን ፈለክ? ማለት ነው ያለብኝ” አለች ለራስዋ::
“ ምን ፈለክ?”
“ ሰዓቴ ተበላሽቶ …” አለ ኦሪዮን::
“ እና ?” አለች ቤርሳቤ ግራ ተጋብታ::
“ ስንት ሰዓት ነው?” ጠየቀ ኦሪዮን :: ሳቅዋን መቆጣጠር አልቻለችም:: ሳያስበው በተናገረው ነገር ሳቁ መጣበት::
“ ስንት ሰኣት እንደሆነ አግኝቼ ብነግርህስ?” አለችው እየሳቀች::
“ በጣም ደስ ይለኛል!” አለ::
“ ስንት ሰሃት ላይ ይመቸኛል ? ቆይ አሁን ስንት ሰዓት ነው?” ብላ ሰአቷን ለመመልከት እጅዋን ለአይንዋ ስታመቻች
“ አራት ከሃያ ” አላት ኦሪዮን:: መቆጣጠር ያልቻለችው ሳቅዋን ለቀቀችው::
No comments:
Post a Comment