Sunday, 27 February 2011

አልተለያይቶም!


                 እሷ
              ሌሊቱን እንቅልፍ ባይኗ ሳይዞር ነው ያደረችው - ቤርሳቤ:: መስታወት ፊት ቆማ የተለያዩ ልብሶቿን እያቀያየረች ትለካለች:: ሁሉም አልስብ አላት:፡ ጥቁር ሱሪ በጥቁር ቦዲ ለብሳ ሰማያዊ ስካርፕ አደረገች:: ይሄ አለባበስዋን እንደሚወደው ብዙ ጊዜ ነግሯታል:: “ አፍ ውስጥ እንደ ሻኛ ስጋ ይሟሟል” ብሎ የሚያወድስላት ከንፈርዋን በስሱ ቀይ ቀለም ቀባችው::
              ለመጨረሻ ጊዜ ራስዋን በመስተዋት ተመለከተች:: የራስዋ መልክ ለራስዋ አማራት:: “በቀጥታ ቢሮው ሄጀ ለምን እንደራቀኝ እጠይቀዋለሁኝ::” አለች:: 
                እሱ
  ከሱፍ /ሙሉ/ ልብሶቹ ውስጥ ነጩን መርጦ በጥቁር ሸሚዝ ለበሰ::  ይሄንን አለባበሱን እንደምትወድለት አስታወሰ:: አግኝቷት ምን ሆና እንደዘጋችው ሊጠይቃት ቆርጧል:: “አምስት ቀን ያለበቂ ምክንያት መዘጋጋት?” አለ በመገረም::
                እነሱ
  የስልኩን መነጋገሪያ  አንስቶ አንድ ሰባት ሁለት ዜሮ ጠቀጠቀ ቁጥሮቹን::
“ሄሎ” የሚል ድምፅ ሰማ:: የቤርሳቤ ድምፅ መሆኑ ገብቶታል::
“እኔ ነኝ” አለ ሳያስበው::
“ምን ፈለክ?” አለችው - ቤርሳቤ:: ከተናገረች በኋላ ሰማያዊ ስካርፕዋን የማትፈልገውን ንግግር ያወጣ አፍዋ ውስጥ ጠቀጠቀችው::
“ምን ፈልጌ ነው ልበላት? ቆይ ለምንድን ነው የተራራቅንው ልበላት? እንዲህ ብላት ደግሞ ፍቅር ፀንቶበት ነው ብላ ትኮራለች” አለ ለራሱ::
“ በአንዴ እሺ ብዬ መገናኘት የለብኝም:: ወንዶች ፊት ከሰጧቸው አይቻሉም:: ኩርፊያዬ ሊገባው ይገባል:: ድምፄን ቆጣ አድርጌ ምን ፈለክ? ማለት ነው ያለብኝ” አለች ለራስዋ::
“ ምን ፈለክ?”
“ ሰዓቴ ተበላሽቶ …” አለ ኦሪዮን::
“ እና ?” አለች ቤርሳቤ ግራ ተጋብታ::
“ ስንት ሰዓት ነው?” ጠየቀ ኦሪዮን :: ሳቅዋን መቆጣጠር አልቻለችም:: ሳያስበው በተናገረው ነገር ሳቁ መጣበት::
“ ስንት ሰኣት እንደሆነ አግኝቼ ብነግርህስ?” አለችው እየሳቀች::
“ በጣም ደስ ይለኛል!” አለ::
“ ስንት ሰሃት ላይ ይመቸኛል ? ቆይ አሁን ስንት ሰዓት ነው?” ብላ ሰአቷን ለመመልከት እጅዋን ለአይንዋ ስታመቻች
“ አራት ከሃያ ” አላት ኦሪዮን:: መቆጣጠር ያልቻለችው ሳቅዋን ለቀቀችው::  

አዳምና ውሻ ሄዋንና ድመት


ግዚአብሄር ጭቃውን አሰማምሮ ሲጨርስ ትኩር ብሎ ተመለከተው::  የሆነ የጎደለው ነገር እንዳለ ገብቶታል:: “ምንድን ነው ይሄ ጭቃ የጎደለው?” አለ እግዚአብሄር:: ጉድለቱ ጎኑ ላይ ወፍራም ጭቃ መሸከሙ ነበር:: ከወፍራሙ ጭቃ ላይ ቆነጠረለት::  የጭቃው እንከን ተቀረፈ:: አዳም አለው ያንን ርጥብ ጭቃ:: ቡጫቂዋ ጭቃም ሄዋንን ሆነች:: አዳምና ሄዋን የገነት ፀሃይ ላይ ተሰጥተው እያለ ውሻና ድመት ወደነሱ መጡ:: የአዳም አይን ሁለቱም እንስሳት ላይ አረፈ:: የሄዋን ቀልብ ግን ድመቲቱ ላይ ነበር:: ድመት ሄዋንን ጠቀስ  አድርጋ ወደ ገነት ዛፎች ስር ይዛት ሄደች:: አዳም እግሩ ስር ተኝቶ ከሚያንኮራፋ ውሻው ጋር ቀረ::    
ድመት አዳም እንዳያይ ደኑ ውስጥ ተደብቃ ለሄዋን የተለያዩ ትምህርቶችን አስተማረቻት:: በችግኞች ተከልላ ተፀዳድታ በእግሮችዋ አፈር ጭራ ሸፍና ለሄዋን አሳየቻት:: ሄዋን ነውርንና ሚስጥርን እንዴት ቀብሮ ማስቀረትና ከሌሎች መደበቅ እንደሚቻል ተመለከተች:: ትምህርት አንድ አለች ሄዋን::
 አስተምህሮ ድመት ሁለት- ድመቲቱ ምራቅዋን የፊት እግሮችዋ መዳፍ ላይ ቀብታ ፊቷን ዳበስ ዳበስ አደረገች:: ሄዋን መዋብን ከድመት ተማረች:: ድመቲቱ ሄዋንን “ተከተዪኝ” ብላ ወደ ጎጆዋ ሄደች:: ትንሽዋ የድመት ጎጆ ሁለት በር ነበራት:: ሄዋን “ይችን ለምታክል ቤት ለምን ሁለት በር አስፈለገ!?” አለች በርጥብ ህሊናዋ:: ለሄዋን ጥያቄ ግን ድመቲቱ ምላሽ ነበራት:: ወንድ ድመቶችን ሊያማልል በሚችል የውብ ኮረዳ ድመት ድምፅ “ሚሚሚያያያውው ውውው” አለች  ድመቲቱ:: አንድ ወደል ድመት ድምፅዋን ሰምቶ መጣ:: የመጣው ወደል ድመት ግን ባልዋ አልነበረም፤ ውሽማዋ እንጂ:: የውሽሜን ነገር ሄዋን ከድመት ተማረች::  በፊት ለፊት የገባው ወደል ውሽሜ ድመት በጓሮ በር ሹክክ ብሎ ሲወጣ ስትመለከት ነው የጓሮ በር ጥቅም ለሄዋን የተገለጠላት:: ሄዋን አንድ ነገር አሰበች “ከአዳም ውጪ ሌላ አዳም ይኖር ይሆን በዚህ ደን!?” ለጥያቄዋ መልስ ባይኖራትም የጓሮን በር ጥቅም በልብዋ አኖረችው:: ወደሉ ድመት አጥር ላይ ተንጠልጥሎ “ሚያው!” አለ በጎርናና የኩራት ድምፅ:: ሄዋን ውሽማን አጥር ማዘለልንም ከድመቲቱ ተማረች:: እነሆ ዛሬ የልጅ ልጅዎችዋ
 መስራቱንማ አቶ ባል ይሰራል
አጥር ዘሎ ሲሄድ ውሽማ ደስ ይላላ”  እያሉ ያንጎራጉራሉ::   
አዳም እግሩ ስር የተኛውን ውሻ ቀስቅሶ አስነሳው::  ውሻው ዞር ዞር ብሎ አካባቢውን ቃኝቶ ተመልሶ ተኛ::  አዳም አካባቢን መጠበቅ እንደሚገባ ከውሻ ተማረ:: ውሻ ወደ አንድ ጥግ ሮጥ ብሎ ሄዶ ሸና አዳም ይሄንንም ከውሻ ተማረ:: ተስተምሮ ሁለት ማለት ነው:: ዛሬ ግን “አጥር ስር የሚሸና ውሻ ነው” ይባላል::
ጆሮውን አቁሞ አፍንጫውን ወጠር ፈታ እያደረገ በእግሮቹ መሬት ጫር ጫር አድርጎ ደመነፍሱ ወደ መራው አቅጣጫ ሮጠ- ውሻ:: ከእንስት ውሺት ጋር ተጣብቆ ነበር የተመለሰው::  አዳም የድመትን አማራጭ አላየምና የውሻን የአደባባይ ምግባር ወረሰ:: ምስጢር እንዴት እንደሚጠበቅ አለማወቁም ጀብደኛ አደረገው:: በሆነ ባልሆነ የሚጮህ ግልፍተኛ:: የውሻን አስተምህሮና የአዳምን ኩረጃ ተደብቃ ትመለከት የነበረችው ድመት እየሳቀች ወደ ሄዋን ሮጠች:: ሳቅዋ ድመትንም ውሻንም አበሳጨ::
በድመቷ ሳቅ የተበሳጨው ውሻ እስዋ ምን የተለየ ጥበብ ብታውቅ ነው ብሎ ተደብቆ ለማየት ወደ ድመት ጎጆ ሄደ:: የድመቲቱን ጎጆ ሲመለከት አንድ ነገር ከነከነው “ለምን የድመቲቱ ጎጆ ሁለት በር ኖረው !?” አለ ውሻ በመገረም በውሻ ህሊናው::  የድመቲቱን የሁለት በር ሚስጥር ለአዳም ነገረው:: አዳም ለጎጆው:: ሄዋን አዳምን እንዴት አሳምና ጎጆዋ ሁለት በር እንዲኖረው እንደምታስደርግ እያሰላሰለች ከፍራፍሬ ለቀማ ስትመለስ አዳምን በኩራት የጓዳ በሩን ተደግፎ ስትመለከተው ሩጫዬን ሮጠልኝ አለች::
የሄዋን አዳዲስ ባህሪዎችን ማምጣት ያላማረው አዳም ድመት ምን እያስተማረቻት እንደሆነ እንዲሰልልለት ውሾን ላከው:: ውሻ ከድመቲቱ ጎጆ ጀርባ ተደብቆ ድመቲቱ ለሄዋን የምታስተምራትን ለመሰለል አደፈጠ:: ድመቲቱን እንጂ ሄዋንን ማየት አልቻለም ነበር:: ሄዋን የአዳምን ተላላኪ ውሻ አይታ ተደብቃ ነበር:: ውሻ አዳም ያዘዘውን ሊያይ ባለመቻሉ ተስፋ ቆርጦ ሊመለስ ሲል ግራ ቀኝ እየተራመደ የሚመጣ ድመት አየ:: የድመቲቱ ባል እንዳልሆነ አውቋል:: ወደሉ ድመት ተገላምጦ ወደ ድመቲቱ ጎጆ ገባ::  ወደሉ ድመት ምን ሊያደርግ ወደ ሌላ ድመወራ /አባወራ እንደማለት/ ቤት እንደገባ ለማየት ውሾ አድብቶ ወደ ድመቲቱ ጎጆ ተጠግቶ አሾለቀ::
በተመለከተው ነገር ደነገጠ:: አዘነም:: አፈረም:: የድመቲቱን ብልግና ማየቱን ነግሮ ሊሳለቅባት እየሮጠ ወደ የፊት ለፊቱ የድመቲቱ በር ሲዞር ውሽሜ ድመት በጓሮ በር ፈትለክ አለ:: ውሻ በፊት ለፊት በር በአይቼሻለሁ ተኮፍሶ ሲገባ ጎጆው ውስጥ ሄዋንና ድመቲቱ ብቻ ነበሩ:: ውሻ ግራ በመጋባት ተዟዙሮ ቤቱ ውስጥ አነፈነፈ:: ጎጆው ውስጥ የተፈጠረውን ሁሉ አይቷል፤ ነገር ግን ድመቲቱ ምንም እንዳልተፈጠረ ተረጋግታ ተቀምጣለች:: ሄዋንም በድመቲቱ መረጋጋት ተገርማ ነበር የምትመለከታት:: ከድመቲቱ እርጋታ የተማረችው ነገር ቢኖር የልብን ሰርቶ ምንም እንዳልተፈጠረ ተረጋግቶ ማሳለፍ እንደሚቻል ነበር:: ውሻም በስተመጨረሻ የገባው ነገር ውሽሜ ድመት በጓሮ በር ማምለጡ ነበር::  የጓሮ በርን ክፋትና የጓሮ በርን ምስጢር ለመንገር ወደ አዳም ሮጠ::
አዳም “አንድ በር ይበቃዋል ለጎጆአችን!” አላት ሄዋንን በጩኸት::  ሄዋን ሳቅ እያለች “ጎጇችን ሁለት በር ይኑረው ያልከው አንተው ነበርክ እኮ አሁን ምን ተገኘና ” አለች ምን ተገኝቶ አንድ በር ይሁን እንዳለ ብታውቅም:: አዳም የሚመልሰው ሲያጣ ውሻን አፍጦ ተመለከተው:: ውሻ ለአዳም የሚመልሰው ሲያጣ መላ ፍለጋ ወደ ድመቲቱ ጎጆ ሮጠ::
የድመቲቱ ጎጆ ሲደርስ የድመቲቱ ባል የጎጆውን አጥር ከፍ አድርጎ እያጠባበቀ ሲያጥር አገኘው:: ውሻ እያለከለከ ተመልሶ ለአዳም ነገረው:: አዳም ከገነት ደን ዛፍ ቆርጦ የጎጇቸውን ክልል አጠረው:: ግቢውን አጥሮ ሲጨርስ አጥሩ በቂ መስሎ አልታይ ሲለው የጓሮ በር አሰርቶ ሃሳብ የጨመረለትን ውሻውን ልጥ አርሶ  ገምዶ አሰረው፤ አጥር የማይመልሰውን ጠላት እንዲጠብቅ:: የውሻም ግቢ ጠባቂነት ያኔ ተጀመረ:: አዳም ጎጆን በአጥር ከልሎ ጠባቂ ውሻ ማሰርን የብልሃት መጨረሻ አድርጎ ቆጠረው:: የረሳው ነገር ግን ነበረ፤ ያም ነገር የሄዋን አማካሪ የሆነችው ድመት ጎጆው ውስጥ መኖሯን ነበር::
ከዚያን ዘመን ጀምሮ ውሻ የጌታው በር ላይ በሰንሰለት ታስሮ በፊት ለፊት ገብተው በጓሮ የሚወጡትን  ውሽሞች እያየ መኖር እጣ ፈንታው ሆነ:: በጓሮ በር የሾለከ ውሽማ ባየ ቁጥር በድመት ተታሎ አዳምን ያሰራው የጓሮ በር ይታሰበውና በእንጉርጉሮ ያለቅሳል:: ያንን ውሻ በማለዳ የሚያሰማውን የፀፀት እንጉርጉሮ ለቅሶ አዳም ከንቱ ማላዘን አለው:: ውሻ ግን ባላዘነ ቁጥር በድመት ተታሎ አዳምን ያሰራው የጓሮ በር የሚያሳየውን ፍቅር አልባ ህይወት እያሰበ እግዚኦልኝ ማለቱ ነው::
ታዲያ ውሻ ጌታው ምን ቢበድለው እንኳን ሊከዳው ይሰንፋል:: የሚያሰንፈው የበደለኝነት ስሜቱ ነው:: ያ የበዳይነት ስሜት የጓዳው በር ጉዳይ ነው:: ውሻ የታማኝነት ምሳሌ ሆኖ በአዳም ግቢ ታስሮ ይኖራል:: ውሻ  በር ላይ ጋደም ብሎ የጌታውን በር መጠበቁ የጓዳ በር ስህተቱን ማካካሻ ታማኝነቱን ማረጋገጡ ነው::
ድመቲቱ ግን የትም ትለምዳለች:: ሁሉ ቤቷ ነው:: በሁሉም የፊት በሮች ገብታ በሁሉም የጓሮ በሮች ትወጣለች:: አጥር ትዘላለች:: ፍፁም በሆነ መመሳሰል የውሽሜዎች አምሳያ ነች:: የቀን መዝመምን አይታ ላትመለስ ከአሳዳሪዎቿ ቤት ትርቃለች:: ልክ ውበት አይቶ የመጣ ውሽማ  ውበት ሲከስም እንደሚሸሸው ማለት ነው:: በውሽሜዎችና በድመቶች መካከል ዘላቂ ፍቅር የለም ዘላቂ ጥቅም እንጂ:: የውሻ ግን ከዚህ ይለያል:: ፍቅሩ እስከ መቃብር ነው:: ታማኝነቱም የዘሩ ነው:: ታዲያ “እንደ ሄዋን

ግንድና ቅርንጫፍ


ስምንት ሰሃት ቀጠሮ ሰባት ሰሃት ላይ ብር የሚያበድረኝ እያፈላለኩ ነበር:: ቆንጆ ልጅ ቀጥሮ ባዶ ኪስ እንደመሆን ምን የምጥ ዘመን ይኖራል!?
‘ፋዘር’ን ስንት ፎግሬ ሃምሳ ብር “እሺ” አስባልኩት:: ለመፅሃፍ መግዢያ ወይም ትምህርት ቤት አዋጡ ተብለን ነው ብለው ኖሮ አይበጥስልኝም ነበረ:: አሪፍ ‘ችክ’ ጠብሼ ነው ስለው እሺ አለኝ:: ግን ልጅቷን ማየት አለብኝ ብሏል:: አይቻት ነው ብሩን የምቦጭቅልህ ብሎኛል:: አንዳንዴ እኮ ‘ፋዘር’ ያበዛዋል:: 
“የቷ ነች?” አለ የማሳየውን ልጅ ከርቀት እየፈለገ:: እንዳታየኝ ተደብቄ  በደንብ ጠቁሜ አሳየሁት::
“ያቺ አንድ ፍሬ ልጅ!?”
ግራ ገብቶኝ “አዎ” አልኩኝ:: እሱ ማዘርን የስንት አመት ጩጬ ሆና እንዳገባት የማላውቅ መስሎታል::
“ እስኪ ጠጋ ብዬ ልያት!” ብሎ እየተጠጋት እየቀረባት ሄደ::  ልጅቷ እየሮጠች ወደኛ መጣች:: “በቀረብኝ ኖሮ ገንዘቡ” አልኩ ለራሴ:: ጓደኛዬ ቢሆን ኖሮ እጣላው ነበር፤ አባቴን ግን ምን ማለት እችላለሁ:: አንዳንዴ  ደግሞ ፋዘር በጣም ያበዛዋል:: የእስዋ እየሮጠች መምጣት ደግሞ አይገርምም::
ልጅት እየሮጠች መጥታ ‘ፋዘር’ ላይ ተጠመጠመችበት:: “ይኸውልሽ ሚጥዬ ስፎክር… ስፎክር ዛሬ ላስተዋውቅሽ አመጣሁት ይሄን ጎረምሳ… ወጠምሻ ወንድም ነው ያለሽ ” ‘ፋዘር’ ማውራቱን ቀጥሏል እኔ ግን ደንግጫለሁም፤ ተናድጃለሁም::
“ትሰማኛለህ!” አለ ‘ፋዘር’ ማታ ቤት ውስጥ ተቀምጠን እያለ:: “እዚህ መንደር ውስጥ አትርመጥመጥ! ማን የማን ልጅ እንደሆነ በማይታወቅበት መንደር ወላጅን ሳያማክሩ ከዛችም ከዛችም ጋር መጋደም አያዋጣም! አባቶቻችን ለምን ይመስልሃል ለልጆቻቸው የትዳር ጓደኛ ይመርጡ የነበረው!? ማን የማን ልጅ እንደሆነ የሚያውቁት እነሱ ብቻ ስለሆኑ ነበር! ትሰማኛለህ ግን?” አለ ጣሪያ ግድግዳውን ስመለከት አይቶ::
“አዎ! ግን እኮ ‘እህትህ ነች እረፍ!’ እያልክ ስታስተዋውቀኝ ይቺ ሶስተኛዋ ሴት ነች… እና እኔ…” ብዬ ልቀጥል ስል “ቀስ በል እናትህ እንዳትሰማ! ምናባክ መንደር ውስጥ ያርመጠምጥሃል!? ወጣ ብልህ አታሽኮረምም? የአባትህ ልጅ እርምጥምጥ! ያውልህ …” ብሎ መቶ ብር ወርውሮልኝ ወጣ::
በሌላ ቀን...
የቀጠሮ ሰሃቴ አልደርስ ብሎኝ እንቆራጠጣለሁኝ፤ ለአራተኛ ጊዜ ሽቶ ተቀባሁኝ - የቀጠሮ ሰሃቴ እስኪደርስ:: “የት ልትሄድ ነው?” አለ ‘ፋዘር’  መቁነጥነጤን አይቶ::
“ፈተና አለብኝ!” አልኩት ደግሞ ልከተልህ እንዳይለኝ:: 
ባክህ እኔን አታታልለኝም በሚል እይታ ተመልክቶኝ  “ በደንብ አዛምደህ ስራ ፈተናህን !... ገባህ አይደል የምልህ ጥያቄውና መልሱ ዝምድና  አላቸው ወይ የሚለውን በደንብ አጢነህ ነው መስራት ያለብህ! ዝም ብሎ ተገኘ ተብሎ …” ብሎ እናቴን በቆረጣ አይቶ ፀጥ አለ::  “እንዲያውም ከፈተና በፊት ለምን ሻይ አልጋብዝህም?...” አላስጨረስኩትም እየሮጥኩኝ ከቤት ወጣሁኝ::
በመንደራችን ያሉ ድብቅ የፋዘር ልጆች ነገር ቢያስጨንቀኝ በመንደራችንና የመንደራችንን አጎራባች መንደር የሚገኙ ሴቶችን መልከፍ አቆምኩኝ:: የዛሬዋን ልጅ ሩቅ ሰፈር ለሌላ ጉዳይ ሄጄ የጠበስኳት ነች::
“ልቀቀኝ እከተዋለሁኝ!” አለች ፎቶዋን ቦርሳዬ ውስጥ ለመክተት እየታገለች:: ፎቶዋን መክተቷ ሳይሆን የቦርሳዬ ባዶነት አሳፍሮኝ ታገልኳት:: ቦርሳዬን ነጥቃኝ ራቁቷን ከአልጋ ላይ ዘላ ወረደች::
“ሹገር ዳዲ!” ብላ ቦርሳዬን በድንጋጤ ጥላው ጮኸች:: “ታውቃቸዋለህ!?” ብላ ቦርሳዬ ውስጥ ያለ ፎቶ አሳየችኝ::
“አዬ ፋዘር!” አልኩ ለራሴ ብቻ በሚሰማ ድምፅ::
“እንዴት አወካቸው!?” አለች ያየችውን ባላመነ አይነት:: መልስ አልነበረኝምና ፀጥ አልኩ:: በልቤ ግን ...
ዱርዬ አባት ያላችሁ
               ዋይ በሉ በግንባራችሁ ተደፍታችሁ!   የሚለውን የካዛንችሱን እብድ የፈረጃን የዘውትር ልፍለፋ እያሰብኩ ነበር:: አንዳንዴ ግን ፋዘር በጣም ያበዛዋል! ለሱ ስል የት ልድረስለት?!      

በፍቅር የተሰበረ ልብዎን ለመጠገን የሚረዱ አምስት ነጥቦች


ፍቅር የደስታና የትፍስህት ምንጭ እንጂ የስብራት ምክንያት እንዲሆን አልተፈጠረም:: ታዲያ ውስጡ ዘልቀን ስንገባ በደስታ የተዋጥነውን ያህል ያፈቀርንው ሰው ሲተወን ልባችን ይሰበርና ቅስማችን ምስቅልቅሉ ይወጣል:: ከፍቅረኛዎ ጋር አብረው እያሉ ያሰቡዋቸው እና የተለሟቸውን ውጥኖች መልሶ ማሰቡ ያምዎታል:፡አሁን እርስዎ ብቻውን የሚበር ርግብ ሆነዋል:: ዘላለም በአብሮነት የሚዘልቅ የመሰሎት የፍቅር ህይወትዎን  በአጭሩ ተቀጭቷልና ሁሉ ነገር የውሸት ይሆንብሆታል:: በዚህ ሰሃት የሚያስቡት ነገር ቢኖር ቁርጥራጭ ትዝታዎችን ከውስጥዎ እንዴት ነቅሰው እንደሚያወጡ ብቻ ነው:: በፍቅር ላይ ፊትዎን ሳያዞሩ የተሰበረ ልብዎን እንዴት ሊጠግኑ እንደሚችሉ ያወጣሉ ያወርዳሉ:: ታዲያ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆነው ደግሞ ወደ ፍቅር ህይወት ውስጥ ለመመለስ ቀርቶ ራሱ ፍቅር መጥቶ የልብዎን በር ቢያንኳኳ ለመክፈት ፈቃደኛ አይሆኑም:: ለምን ቢሉ የተነጠቁት የፍቅር ህይወት “ፍቅር” የሚባለውን እሳቤ ጥላሸት ቀብቶታልና ነው:: በዚህ ስሜት ውስጥ ሆነው ከዘለቁ ምናልባትም ለህይወትዎ የሚመች ጥሩ አፍቃሪ ቢያገኙ እንኳን ዳግም ልብዎን ሊሰጡት አይፈቅዱም:: ግና ውስጥዎ ዳግም ታድሶ የልብዎ በር ለፍቅር ክፍት ይሆን ዘንድ የተሰበረ ልብዎን የሚጠግኑባቸው አምስት ጤናማ መንገዶች አሉና ይሞክሯቸው::
ልብዎ ከፍቅረኛዎ መለየቱን አምኖ እንዲቀበል ያድርጉ
ልብዎን ከፍተው የሰጡት ሰው ቢከዳዎት አለም ሁሉ የከዳዎት አይምሰሎት:: ወደ ኋላ መለስ ብለው ከፍቅረኛዎ ጋር ያሳለፉዋቸውን ወርቃማ ጊዜያት ማሰቡ ውስጥዎን በሰቀቀን ሊጨርስ እንደሚችል ግልፅ ነው:: ታዲያ ይህ ስሜት እያደር ውስጥዎ ዘልቆ ሙሉ በሙሉ ከአለም የተገለሉ ብቸኛ ፍጡር ሊያደርጎት እንደሚችል አይርሱ:: ስለዚህ ባሳለፉት መጥፎ ትዝታ ተገፍተው ብቻዎትን ሊቀሩ አይገባም:: ከዚህ ይልቅ ውስጥዎን ያቆሰለውን የመለየት ህመም ፊት ለፊት ተጋፍጠው ካለፈው የሚማሩበትን ቀና መንገድ መጓዙ ይሻላል:: እንዲህ ባለው ሁኔታ በእያንዳንዱ ትዝታዎ ላይ የበላይ መሆንዎ ለቀጣይ ህይወትዎ የሚያምንና የሚያፈቅር ሙሉ ልብ እንዲኖሮት ያደርጋል:: አንድ ነገር አይርሱ ዛሬ ያልተጋፈጡት የሚያምር የፍቅር እውነታ ነገ ፍርሃትን ይወልዳል:: ፍርሃት ደግሞ እምነትን ያጠፋል:: እምነት የሌለው ልብ ደግሞ ሊያፈቅር አይቻለውም:: በዚህ ሰሃት እውነትን ሲጋፈጡ አቅም ሊያንሶትና ደጋግመው ወደ ውስጥ ሊያለቅሱ ይችላሉ:: ግን ነገ ጥሩ አፍቃሪ የሚሆነው ልብዎ ያመሰግኖታል::
ንዴትዎን የሚያበርዱበት ጤናማ መንገድ ይፈልጉ  
አሁን ማድረግ የሚፈልጉትን ጠንቅቀው ያውቃሉ:: ግን እንዴት ማድረግ እንዳለብዎት ግልፅ መንገድ አላገኙም:: አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች ጋር ተቀላቅለው ደስተኛ ለመምሰል ከመታገል እቤትዎ ቁጭ ብለው ቴሌቪዥን ላይ ማፍጠጥ ሊቀሎት ይችላል:: ይሄ አንዳንዴ ከራስዎ ጋር ለመነጋገር ስለሚረዳ ጥሩ ቢሆንም ማህበራዊ ግንኙነትዎን ማጠንከሩ ግን በውስጥዎ ሰላም ለመፍጠር ስለሚረዳዎት አስፈላጊ ነው::  ወደዱም ጠሉም ከጓደኞችዎ ጋር መገናኘትዎ ከፍቅረኛዎ ጋር በመለየትዎ የደረሰብዎትን ጭንቀት ለማስወገድ ይረዳዎታል:: እንዲህ የተለያዩ አጋጣሚዎችን ተጠቅመው ጊዜዎትን ከሰዎች ጋር ማሳለፍ በጣም ተመራጭ ነው:: ጭንቀት ወደ ተስፋ መቁረጥ እንደሚያመራ አይርሱ:: ተስፋ መቁረጥ ደግሞ ወደ ንዴት አምርቶ አጉል ያደርጋል:: ከፍቅረኛዎ ጋር መለየትዎ እንዲያሸንፍዎት አይፍቀዱ:: የካደዎት ፍቅረኛዎ ደህና መሆንዎን በሚገባ ሊያውቅ ይገባል:: ነገሩ ነው እንጂ… አይነት መሆኑ ነው::
ለራስዎ ክብር ይኑርዎት
ፍቅረኛዎ በእርስዎ ላይ ኃይል የሚኖረው እርስዎ የሰጡትን ያህል ነው:: ከተለያዩ በኋላ ስለራስዎት መጥፎ ካሰቡና ራስዎን ከጣሉ ከፍቅረኛዎ መለየቱ ልብዎን ብቻ ሳይሆን ነፍስዎትንም አኝኮ በልቶታል ማለት ነው:: ለሁሉም ጊዜ አለውና ከጊዜ ጋር የተሰበረ ልብዎ አብሮ ይጠገናል:: መንፈስዎና ነፍስዎ ከውስጥዎ ከጠፋ ግን መልሶ ማግኘቱ አስቸጋሪ ነው:: ሁልጊዜ ደስታ ይሰማዎት:: ፈገግታ ከፊትዎ አይጥፋ:: ለራስዎ ያልዎትን ፍቅር በተለያየ መንገድ ይግለፁ:: በጎ በጎ ነገሮችን ያስቡ:: አንድ ነገር ደጋግመው ለራስዎ ይንገሩት፤ ከከዳዎት ፍቅረኛዎ ውጪ ሙሉ ሰው ሆነው ሊኖሩና ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ መሆንዎን::
ውስጥዎ ያለውን ስሜትዎን ከሰው ጋር ያውሩት  
በጣም አስቸጋሪው ነገር ህመምዎን ውስጥዎ አፍነው መያዝዎ ነው:: በውስጥዎ ታፍነው የሚቀመጡ የሚጎዱ ሃሳቦች ያስጨንቃሉ፣ ግራ ያጋባሉ፣ ያናድዳሉ:: ብቸኛ ያደርጋሉ:: የተለይዎት ፍቅረኛዎ ለእርስዎ ምን ማለት እንደሆነ ሊገባው ለሚችል ጓደኛዎ ጉዳዩን ያውሩ:: ስሜትዎን እንዲህ ሲገልፁ የልብ ስብራትዎ ያገግማል:: ከሚወዱት ሰው መለየትዎ በውስጥዎ የፈጠረውን ስሜት ለጓደኛዎ ሳይደብቁ ይንገሩ:: ከዛ መጥፎ ስሜት ለመውጣት እያደረጉ ያሉትን በጎ እርምጃዎችም ይንገሩዋቸው:: እንዲህ ራስዎን ለጓደኛዎ ግልፅ አድርገው ሲቀርቡ ጓደኛዎትም በተመሳሳይ ስሜት ውስጥ አልፎ  ሊሆን ስለሚችል ተጨባጭ የሆነ ምክር ሊሰጥዎት ይችላል:: ይሄ ደግሞ የተሰበረ ልብዎን ለመጠገን ወሳኝ ሚና አለው::
ራስዎን አይደብቁ   
ራስዎ ሲረጋጋና ውስጥዎ ዝግጁ ሲሆን ልብዎን ለፍቅር ክፍት ያድርጉ:: ምናልባት ከአዲስ ሰው ጋር ለመጀመርያ ጊዜ ሲገናኙ ውስጥዎ ሊጎዳ ይችላል::ምናልባትም አዲስ የተዋወቁትን ሰው ከቀድሞ የፍቅር ታሪክዎ አንፃር እየመዘኑት ተመሳሳይ እጣ የሚጠብቅዎት እየመሰሎት በጭንቀት ሊሰቃዩ ይችላሉ:: ይሄ አዲስ ነገር ስላልሆነ ብዙ ሊያስጨንቆት አይገባም:: ዋናው መርሳት የሌለብዎት ቁምነገር ትናንት ማለፉን ነው:: ያለፈው ፀፀትዎ የሚከተልዎ ከሆነ ግን ሁሉንም ሰው በአንድ መነፅር ነው የሚያዩት:: ሰውን ለመገመት አይቸኩሉ:: በራስዎ ውስጥ ያለ አንዳች ልዩ ነገር ያንን ሰው ለፍቅር እንደሚጋብዘው አይርሱ:: አብረው ሊሆኑት ስላሰቡት ሰው ስብዕና ለማወቅ ጊዜ ይውሰዱ:: ምናልባት ብዙ የሚጋሯቸው ተመሳሳይ ስሜቶች ሊኖሩ ይችላሉ:: ነገሮች ከዚህ ተነስተው ወዴት ሊወስዱዎት እንደሚችሉ ማን ያውቃል!?
እናም የፍቅር ቁስለኞች የተሰበረ ልብን በመጠገኑ ሂደት ውስጥ ማለፉ ሊከብዳቸው ይችላል:: ዋናው ቁም ነገር ግን ሙሉ ፈቃደኝነትና ከልብ የመነጨ ፍላጎት ብቻ ነው::